ታሪክ
የጋምቤላ ከተማ አመሠራረት እንደ እ.ኤ.አ. ግንቦት 15/1902 በኢትዮጵያ መንግሥት በዳግማዊ አፄ ምኒልክ እና በእንግሊዝ መንግስት መካከል በተፈረመው ስምምነት ሲሆን የመልክዓ ምድራዊ አቀማመጧ ከአዲስ አበባ በደቡብ ምዕራብ አቅጣጫ ትገኛለች፡፡ የጋምቤላ ከተማ በሁለት አቅጣጫዎች ከአዲስ አበባ በጎሬ አቅጣጫ በ766 ኪሎ ሜትር እና በጋምቤላ ደንቢዶሎ ወለጋ በኩል በ666 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡
የጋምቤላ ከተማ አቀማመጥ ሜዳማ እና አነስተኛ ጋራዎች ያሉባት እንዲሁም በባሮ ወንዝ ዳር የሚትገኝ በመሆኗ ለወደፊት እድገቷ ከፍተኛ ነው፡፡ የባሮ ወንዝ ከተማዋን መሀል ለመሃል ሰንጥቆ የሚፈስ በመሆኑ ለከተማዋ ትልቅ የልማት ሀብት ነው፡፡
የጋምቤላ ከተማ የአየር ፀባይ አማካይ የሙቀት መጠን 28.3 ዲግሪ ሴልሺየስ ያላት ብትሆንም ማንኛውም የከተማዋ ነዋሪ በሚኖርበት አከባቢ በመንገድ ዳር እንዲሁም በመኖሪያ ቤት አከባቢ ዛፍ የመትከል ልምድ ስላለው ዓመቱን በሙሉ በአረንጓዴ የተሸፈነች ነች፡፡
በጋምቤላ ከተማ አምስት ነባር ብሔረሰቦች ሲኖሩ በተጨማሪም ከመሀል ሀገር የመጡ የተለያዩ ብሔረሰቦች በከተማዋ ተሰበጣጥረው በመፈቃቀር እና በመከባበር በሠላም አብረው የሚኖሩባት የብሔር ብሔረሰቦች ከተማ ናት፡፡
የጋምቤላ ከተማ ከባህር ጠለል በላይ ከ400- 500 ሜትር ከፍታ ላይ የሚትገኝ ሲሆን የዝናብ ስርጭቱ እንደ ወቅቱ መጠንና ስፋት የሚለያይ ቢሆንም ከግንቦት እስከ ጥቅምት ባሉት ወራት የዝናብ ወቅት ሲሆን ዓመታዊ የከተማዋ የዝናብ መጠን 1036.9 ሚሊ ሜትር ይደርሳል፡፡